ሃይናን
ሃይናን (ቻይንኛ፦ 海南 ወይም /ሓይናም/) በደቡብ ቻይና ባሕር የሚገኝ የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ ታላቅ ደሴትና ክፍላገር ነው።
የሃይናን ትርጉም «ከባሕር ደቡብ» ነው። የሃን ቻይናውያን ሰዎች ከ118 ዓክልበ. ጀመሮ ሠፈሩበት። አሁን 84% ይቆጠራሉ። ከነርሱ ቀድሞ የኖሩበት ኗሪዎች ሊ ብሔር ወደ ደቡብ ይገኛሉ፣ 15% ናቸው። የሁላቸው መደበኛ ቋንቋ ፑቶንግኋ ቻይንኛ ሲሆን፣ ቻይናውያን ደግሞ ሚንኛ (ሃይናንኛ)፣ ሊ ብሔርም ደግሞ ሕላይኛ ይናገራሉ። ባብዛኛው የደሴት ኗሪዎች የቡዲስም ምዕመናን ሲሆኑ፣ አንዳንድ እስላም ወይም ክርስቲያን ይገኛሉ። ዋናው ሰብል ሩዝ፣ ከዚያም ኮኮነት ዘምባባ፣ ቃጫ፣ አናናስ፣ ቁንዶ በርበሬ፣ ሻይ፣ ቡና፣ ሸንኮራ አገዳ፣ ጎማ ዛፍ ሁሉ ይታረሳሉ። የሃይናን ቢጫ ፋኖስ ሚጥሚጣ ለሃይናን ደሴት ብርቅዬ የቻይና ሚጥሚጣ አይነት ነው። ለማዳ እንስሶች በተለይ ፍየል፣ በሬ፣ የውሃ ጎሽ፣ ዶሮ፣ ዚዪ፣ ዳክዬ አላቸው።
ሃይናን በጣም ትልቅ የቱሪስም መድረሻ ሆኗል፤ በቅርብም የቻይና መንግሥት መላው ክፍላገሩ «ዓለም አቀፍ ነጻ ንግድ ክልል» እንዲሆን ለማድረግ እያቀደ ነው።
የሃይናን ባህል ስለ አበሳሰሉ ይታወቃል፤ በተለይ የበግ፣ ሠርጣን፣ ዳክዬ፣ ዶሮ፣ ዚዪ፣ አሳ፣ አሳማ አሠራሮች አላቸው። «የሃይናን ዶሮ በሩዝ» የሚል አሠራር በመላው ደቡብ-ምሥራቅ እስያ በተለይም በሲንጋፖር የተወደደ ሆኗል።
በሃይናን ደሴት ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ አትክልትና እንስሳት ዝርዮች አሉበት። በተለይም
ከአትክልት፦
- የሃይናን ቢጫ ፋኖስ ሚጥሚጣ የCapsicum chinense አይነት
- የሃይናን ነጭ ጥድ Pinus fenzeliana
- የሃይናን ዝግባ Cephalotaxus hainanensis
ከእንስሳት፦
- የሃይናን ጸጉራም ትድግ Neohylomys hainanensis
- የሃይናን ቆቅ Arborophila ardens
- የሃይናን ጣዎስ Polyplectron katsumatae
- የሃይናን ጥቁር-ጉትያ ጊቦን ጦጣ Nomascus hainanus
- የሃይናን መንትሌ Lepus hainanus
- የሃይናን ነብር-ድመት Prionailurus bengalensis alleni የነብር-ድመት ንዑስ ዝርያ ነው።
- የሃይናን ቅጠል ተንጫጪ ወፍ Phylloscopus hainanus